Thursday, 15 August 2019 08:34

ሐረሪ ክልል የተከሰተውን አተት በሽታ ለመቆጣጠር የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ ገለጸ።

Rate this item
(0 votes)

የጤና ኤክስቴንሽንና የጤና ባለሞያዎችን ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ በመስራት በሽታው እንዳይስፋፋ እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን የወረዳ ጤና ተቋማት ሐላፊዎች ይገልጻሉ።

በቢሮው የህብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አሰፋ ቱፋ እንደገለጹት ባለፉት ሁለት ወራት በአጎራባች ከተሞች የታየው አተት በሽታ ወደ ክልሉ እንዳይዛመት በርካታ ስራዎችን ቢከናወኑም በአሁኑ ወቅት በክልሉ የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት(አተት) በሽታ ምልክት ታይቷል።

በዚህም የበሽታው ጥርጣሬ የታየባቸውን 11 ሰዎችን ምርመራ በማድረግ በ6ቱ ላይ በሽታው ሙሉ ለሙሉ ሊገኝ መቻሉን ተናግረዋል።

በሽታው የተከሰተባቸውን ስፍራዎች በመለየት ለህብረተሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት በመስጠት በሽታው ወደ ሌላ አካባቢ እንዳይዛመት የመከላከል ስራ እየተሰራ ይገኛል።

በበሽታው ለታያዙ ሰዎችም በከተማና ገጠር ጤና ተቋማት ውስጥ በተዘጋጁ የህክምና ስፍራዎች ህክምናና የተለያዩ የድጋፍና እንክብካቤ አገልግሎት አግኝተው ወደ መጡበት አካባቢ መመለሳቸውን ተናግረዋል።

ቢሮውም አስፈላጊ የሆኑ የህክምና ቁሳቁሶችና ባለሞያዎችን በስፍራው ላይ በማሟላት በሽታውን የመቆጣጠር ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አቶ እሸቱ ጠቁመው ህብረተሰቡም የአካባቢና ግል ንዕህናን መጠበቅ እንዲሁም አትክልትና ፍራፍሬን አጥቦ መመገብና ውሃን አክሞ መጠቀም እንደሚገባና የበሽታው ምልክት ሰያጋጥምም ወደ ጤና ተቋም በመምጣት ህክምናውን በነጻ ማግኘት እንደሚችሉ ተናግረዋል።

ወቅቱ ክረምት ከመሆኑ አንፃርና ምልክቱም እየታየ በመሆኑ በወረዳው አስፈላጊው የህክምና ባለሞያዎችንና መድሃኒት በሟሟላት ህመምተኛው ተለይቶ የሚታከምበት ቦታ መዘጋጀቱን የገለጹት የኢሚር ኑር ወረዳ ጤና ጣቢያ ሐላፊ አቶ አብዱላዚዝ ሳሊህ በአሁኑ ወቅት በክልሉ በሌሎች ስፍራዎች የተከሰተው የአተት በሽታ በወረዳው አለመከሰቱን ተናግረዋል።

ህብረተሰቡ የአትክልትና የፍራፍሬ ምርት አጥበው እንዲሁም ጥሬ ስጋን እብስሎ እንዲመገብ ለማድረግና ግንዛቤ ለማስጨበጥ የጤና ባለሞያዎችና የጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞች ቤት ለቤት በመዞር እያስተማሩ እንደሚገኙም ተናግረዋል።

የበሽታው ምልክት ከታየባቸው አንዱ የሶፊ ወረዳ ሲሆን የአተት በሽታ እንዳይስፋፋ ህብረተሰቡን በየመንደሩ የማስተማር፣ የመድሃኒትና የባለሞያ አቅርቦት የማጠናከር ስራ በቅንጅት እየተሰራ ነው ያሉት በወረዳው የሚገኘው የሐረዌ ጤና ጣቢያ ሐላፊ አቶ ጠሃ አብዶሽ ናቸው።

Read 363 times